የአባላዘር በሽታዎች ምንድን ናቸው ?
የአባላዘር በሸታዎች ማለት በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም በጠለቀ አካላዊ ንክኪ የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው ፡፡
ለአባላዘር በሽታዎች ምን ያህል ተጋላጭ ነኝ?
ግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ለአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭ ቢሆንም የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች(ጌይ)፣ሁለቱንም ጾታ አፍቃሪዎች(ባይሴክሽዋል) እና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚየደርጉ ወንዶች (ኤምኤሰኤም) ግን በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው፡፡ከፍተኛ የቂጥኝ ሕመም ቁጥር ከመኖሩ በተጨማሪ ግማሽ የሚሆነው የኤችአይቪ ቫይረስ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚየደርጉ ወንዶች (ኤምኤሰኤም) ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡
የአባላዘር በሽታዎች እንዴት ይተላለፋሉ?
የአባላዘር በሽታዎች የአባላዘር በሽታ ከያዘው ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በወሲብ ወቅት ይተላለፋሉ ይህም በአፍ፣በፊንጢጣ እና በሴት ብልት በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እና የመራቢያ አካላት የቆዳ ንክኪን ያጠቃልላል፡፡
እንደ ጨብጥ፣የኤችአይቪ ቫይረስ እና ክላማይዲያ የመሳሰሉት በብልት አካል ፈሳሾች የሚተላለፉ ናቸው፡፡ የኤችአይቪ እና ሔፒታይተስ ቢ ቫይረስ ደግሞ በደም ይተላለፋሉ፡፡ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች እንደ ቂጥኝ፣ ጄኒታል ኸርፕስ እና ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመሳሰሉት ደግሞ በቆዳ ንክኪ የተላላፋሉ፡፡
የአባላዘር በሽታ እንዳለብኝ በምን አውቃለሁ?
አብዛኛዎቹ የአባላዘር በሽታዎች ምልክት የማያሳዩ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሳናውቀው ሕመሙ ሊይዘን ስለሚችል ማረጋገጥ የምንችለው ምርመራ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ እንደ ኸርፕስ ያሉት የአባላዘር በሽታዎች የኤችአይቪ ቫይረስ እንዲተላለፍ አመቺ መንገድ ስለሚፈጥሩ የራስን እና የፍቅር ጓደኛን ጤንነት ቅድሚያ በመመርመር መጠበቅ ይቻላል፡፡ ማንኛውም የወሲብ ግንኙነት የሚያደርግ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ(ጌይ)፣ሁለቱንም ጾታ አፍቃሪ (ባይሴክሽዋል) እና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ወንዶች (ኤምኤሰኤም) የማኅበረሰብ ክፍሎች ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ምርመራዎች እንዲያደርጉ ይመከራል
- የኤችአይቪ ቫይረስ ምርመራ በአመት አንዴ፡፡
- የቂጥኝ (Syphilis) ምርመራ፡፡
- የሔፒታይተስ ቢ ቫይረስ ምርመራ፡፡
- የሔፒታይተስ ሲ ቫይረስ ምርመራ እንደ ግለሰቡ ተጋላጭነት፡፡
- የፊንጢጣ፣የጨብጥ እና የክላማይዲያ ምርመራ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከታ ወይም ቦተም ሆነን በፊንጢጣ በኩል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካደረግን፡፡
- የሽንት ቧንቧ፣የጨብጥ እና የክላማይዲያ ምርመራ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከላ ወይም ቶፕ ሆነን በፊንጢጣ በኩል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካደረግን ወይም በአፍ (ኦራል ሴክስ) የወሲብ ግንኙነት በወሲብ ጓደኛችን ከተደረገልን፡፡
- የጉሮሮ፣የጨብጥ ምርመራ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በአፍ (ኦራል ሴክስ) ወሲብ ግንኙነት ለወሲብ ጓደኛቸን ካደረግን ይህም በወንድ ብልት፣ በሴት ብልት እና ፊንጢጣላይ ሊሆን የችላል፡፡
- በመጨረሻም በሐኪማችን የኸርፕስ ምርመራ ሊታዘዝል ይችላል ፡፡
የአባላዘር በሽታን መታከም ይችላል ?
አንዳንድ የአባላዘር በሽታዎች እንደ ቂጥኝ፣ ጨብጥ እና ክላማይዲያ ያሉት የአባላዘር በሽታዎች በመድኀኒት የሚድኑ ሲሆን ይህም የሚሆነው የወሲብ ጓደኛችንም ተመርምሮ እና የታዘዘልንን መድኀኒት ጨርሰን ስንወስድ ነው፡፡ ነገር ግን ከዳንን በኋላ ጥንቃቄ የጎደለው ወይም የአባላዘር በሽታ ከያዘው ሰው ጋር የወሲብ ግንኙነት ካደረግን ለአባላዘር በሽታ በድጋሜ ተጋላጭ መሆናችንን መገንዘብ አለብን፡፡
ከአባላዘር በሽታ እራሴን እንዴት መከላከል እችላለሁ?
ማንኛዉም ግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርግ ሰው ለአባላዘር በሽታ ተጋላጭ መሆኑን በቅድሚያ መገንዘብ አለበት ነገር ግን የአባላዘር በሽታዎችን መተላለፍያ መንገድ ግንዛቤ በመያዝ እንዴት መከላከል እንዳለብን ማወቅ እንችላለን፡፡
- ክትባት በመውሰድ ማንኛውም የወሲብ ግንኙነት የሚያደርግ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ(ጌይ)፣ሁለቱንም ጾታ አፍቃሪ (ባይሴክሽዋል) እና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ወንዶች (ኤምኤሰኤም) ማኅበረሰብ ክፍል ለ ሄፕታይተስ ቢ፣ሄፕታይተስ ሲ እና ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ከፍተኛ ተጋላጭነት ስላላቸው የሄፕታይተስ ቢ እና የሄፕታይተስ ሲ ክትባት እንዲወስዱ ይመከራል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም እድሜው ከሃያ ስድሰት (፳፮) ዓመት በታች ያለ የዚህ ማኅበረሰብ የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት በተጨማሪ እንዲወስድ ይመከራል፡፡
- በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግ እና ክትባት መውሰድ ጠቃሚ ሆኖ ሳለ በተጨማሪ ደግሞ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ማስተዋለ ይገባል፡፡
- ከየትኛውም አዲስ የወሲብ ጓደኛ ጋር በግልጽ ስለ አባላዘር በሽታዎች መወያየት እና አብሮ መመርመር ያስፈልጋል
- ኮንዶምን ከ ውሃ ነክ ማለስለሻዎች ጋር በአግባቡ እና በዘላቂነት መጠቀም
- ከግንኙነት በፊትም ሆነ በግንኙነት ወቅት አልኮል እና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን ከመጠቀም መቆጠብ ምክንያቱም አልኮል እና ሌሎች አደንዛዥ እጾች የማመዛዘን ችሎታችንን ስለሚያደክሙ አላስፈላጊ ለሆነ ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያጋልጡናል፡፡
- የወሲብ ጓደኛ ቁጥራችንን መቀነስ ይህም በአንደ የወሲብ ጓደኛ ብንወሰን ከሁሉ በላይ ተመራጭ ነው፡፡

