ከኤችአይቪ ጋር መኖር
የፀረ ኤችአይቪ እና ተጓዳኝ የሕክምና አገልግሎት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ እና እየተስፋፋ በመምጣቱ በአሁኑ ሰአት ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በጤንነት ለረጅም እድሜ ይኖራሉ፡፡ የዛሬው ጽሑፍም ይህንን በተመለከተ ይሆናል፡፡
ጤናን መጠበቅ
የመጀመርያው ውሳኔ የሚጀምረው ከተመረመርን በኋላ ወድያዉኑ የፀረ ኤችአይቪ መድኀኒቶችን መውሰድ መጀመር ነው፡፡ ይህም ባለፈው እንደገለጽነው የሰውነታችንን በሽታን የመከላከል አቅምን በመጨመር በደማችን ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ ቁጥር መቀነስ እንችላለን፡፡
መድኀኒትን ዘወትር እና በአግባቡ ከመውስድ በተጨማሪ የማያቋርጥ የሕክምና ክትትል ማድረግ አለብን፡፡
መናገር
ለፍቅር ወይም ለወሲብ ጓደኛችን ስለ ኤችአይቪ ውጤታችን መናገር አስፈላጊ ነው ይህም ቫይረሱን እንዳናስተላፍ የሚረዱንን ቅድመ ጥንቃቄዎች እንድናደርግ እና በጋብቻ እንድንወስን ያስችለናል፡፡
የሌሎችን እርዳታ ማግኘት
የኤችአይቪ ቫይረስ በደማችን ውስጥ እንዳለ በሚነገረን ሰአትም ሆነ መድኀኒቱን ስንጀምር ለተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች ልንጋጥ እንችላለን ለዚህም ለቅርብ ዘመድ ወይም ጓደኛ በመንገር እርዳታ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክትትል በምናደርግበት የጤና ተቋም ውስጥ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው በሚገኝ ሰዎች የተቋቋሙ የእርስ በርስ መረዳጃ ቡድኖች ውስጥም በመሳተፍ ችግሮችን ማቅለል ይቻላል፡፡
ለተጓዳኝ በሽታዎች ሕክምና ማድረግ እና የሌሎች ተጋላጭነትን መቀነስ
ከኤችአይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎችን እና አባላዘር በሽታዎችን በጊዜ መታከም የራስን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ቫይረሱ ወደ ወሲብ ጓደኛችን እንዳይተላፍ ይጠቅማል፡፡

