እከክ(scabies)
እከክ በአይን በማይታዩ ነፍሳት የሚመጣ የቆዳ ሕመም ሲሆን በሽታውም የሚከሰተው እነዚህ ነፍሳት የላይኛውን የቆዳ ክፍል በመቦርቦር እንቁላላቸውን እየጣሉ በሚኖሩበት ወቅት ነው፡፡
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
- ከፍተኛ የሆነ የቆዳ ማሳከክ በተለይ በምሽት ጊዜ በእጅ አንጓ፣ ክርን፣ ብብት፣ በጣቶች መሃከል፣የጡት ጫፍ፣ ብልት፣ ወገብ እና መቀመጫ አካባቢ በአብዛኛው ከፍተኛ የሆነ የቆዳ ማሳከክ በተለይ በምሽት ጊዜ መኖር፡፡
- ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች እና በሰውነት ላይ ጥቃቅን እብጠቶች መታየት፡፡ እነዚህ እብጠቶችን ማከክ ቁስል እንዲፈጠር እና ተቀጽላ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል፡፡
ምልክቶቹ በምን ያህል ጊዜ ይታያሉ?
ከዚህ በፊት በሕመሙ የተጠቃ/ች ከሆነ እስከ አራት ቀናት ባሉት ቀናት ውስጥ ምልክቱ ይታያል፡፡ ነገር ግን ለሕመሙ አዲስ የሆነ/ች ታማሚ ምልክቶቹ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ፡፡
እከክ ወይም እስኬቢስ እንዴት ይተላለፋል?
የእከክ በሽታ አምጪ ነፍሳት በቀጥታ የቆዳ ንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን የቆዳ ንክኪውም ረዘም ላለ ጊዜ መሆን አለበት፡፡በአዋቂዎች ላይ በአብዛኛው የሚተላለፈው በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ነው፡፡ አልባሳት፣ፎጣ፣አንሶላ እና የመሳሰሉትን ሕመሙ ካለበት ሰው ጋርም በመጋራትም ይተላለፋል፡፡
ሕክምናው ምንድን ነው?
የበሽታውን አምጪ ነፍሳት እና እንቁላላቸውን የሚገድሉ ቅባቶች በሐኪም ትእዛዝ ማግኝት ይቻላል፡፡መድኀኒት ከታዘዘልን በኋላ በታዘዘልን መሰረት በጠቀም አለብን፡፡ ከመድኀኒቱ በኋላ ንጹህ ልብስ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡በበሽታው ተይዘን መድኀኒት በሐኪም ከታዘዘልን የፍቅር ጓደኛችን እና አብረውን የሚኖሩ ጓደኞቻችንም መድኀኒቱን ለእነርሱም ታዝዞ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
የእከክ አምጪ ነፍሳትን እንዴት ከአልባሳት ላይ ማስወገድ እችላለው?
አልባሳት፣ፎጣ፣አንሶላ እና የመሳሰሉትን በፈላ ውሃ በመዘፍዘፍና በማጠብ ለሦስት ቀናት ከቆዳ ንክኪ ማራቅ፡፡በተፈጥሮ እነዚህን ነፍሳት ከሰው ቆዳ ውጭ ከሦስት ቀናት በኋላ መኖር ስለማይችሉ አልባሳትን ለሶስት ቀን ከቆዳ ንክኪ ማራቅ አስፈላጊ ነው፡፡

