በአማካኝ 16 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በሕይወት ዘመኑ/ኗ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ለድብርት ይጋለጣሉ፡፡ ድብርት ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ማለትም ሕፃናት፣አዋቂ እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ያጠቃል፡፡
የድብርት መምጫ መንገዶች
የድብርት መምጫ መንገዶች እንደየ ግለሰቡ የተለያዩ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ ምክንያቶች በአንድ ላይ በመሆን ድብርትን ይቀሰቅሳሉ፡፡ እነዚህም ምክንያቶች ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው
- በቤተሰብ የዘር ሐረግ ውስጥ ከዚህ በፊት የድብርት ታማሚ ካለ፡፡
- ጉዳት እና ጭንቀት ይህም የትዳር ፍቺ ወይም የፍቅር ግንኙነት መቋረጥ፤ የቅርብ ሰው ሞት እና የገንዘብ ችግር የመሳሰሉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መልካም አጋጣሚ የምንላቸው እንደ አዲስ ስራ እና ትዳርም ለድብርት ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡
- ስለወደፊት መልካም ነገር ያለማሰብ ግለ ባሕሪ ይህም ለራስ ካለን ዝቅተኛ አመለካከት ጋር ተዳምሮ ሊሆንም ይችላል፡፡
- እንደ የልብ ሕመም፤ ካንሰር፣ ኤችአይቪ ኤድስ እና የተለያዩ ሕመሞች፡፡
- የመድኀኒት የጎንዮሽ ጉዳት፡፡
- ሌሎች የአእምሮ ሕመሞች እንደ ጭንቀት፣የአመጋገብ ሰርአት መዛባት፣ ሱሰኝነት እና አንዳንድ የስነ ልቦና ሕመሞች፡፡
የድብርት ምልክቶች
ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ምልክቶች በተከታታይ ለሁለት ሳምንት በላይ ከታየብን በድብርት እንደተጠቃን ማሳያ ይሆናል፡፡
- መከፋት፣የሐዘን እና የባዶነት ስሜት፡፡
- በቀላሉ ማልቀስ፡፡
- የዘወትር ተግባራትን የማከናወን ፍላጎት ማጣት፡፡
- ሁሉም ተግባራት አድካሚ መስሎ መታየት፡፡
- በሁሉም ነገር ደስታን ማጣት፡፡
- ድካም እና ጉልበት ማጣት፡፡
- እራስን መውቀስ እና ዋጋ ቢስ የመሆን ስሜት፡፡
- የአእምሮ እረፍት ማጣት እና በቀላሉ መበሳጨት፡፡
- በተደጋጋሚ በጎ ነገርን አለማሰብ፡፡
- የአመጋገብ ስርአት መዛባት ይህም ክብደት መጨመር ወይም መቀነስን ሊያስከትል ይችላል፡፡
- የእንቅልፍ ኡደት መዛባት ይህም የእንቅልፍ እጦት ወይም አብዝቶ መተኛት ሊሆን ይችላል፡፡
- የወሲብ ፍላጎት መቀነስ፡፡
- በሕክምና ሊድኑ ያልቻሉ የሰውነት ሕመም ምልክቶች፡፡
- የብቸኝነት እና የመገለል ስሜት፡፡
- እራስን የማጥፋት የአስተሳሰብ ዝንባሌ ፡፡
በድብርት ጊዜ እንዴት እራስን መርዳት ይቻላል
- የምንወደውን ተግባራት የዘወትር ልምድ ማድረግ ፡፡
- ለብቻ መሆንን ማስወገድ በዚህ ሊረዱን ይችላሉ የምንለውን የቅርበ ሰው ስላለንበት ሁኔታ ማማከር፡፡
- በእራሳችን ጫና የሚፈጥሩብንን ተግባራት እና ሃላፊነቶችን መቀንሰ ወይም ማስወገድ፡፡
- የስራ ጫናዎችን መቀነስ እና ዘና ለማለት መሞከር፡፡
- ስለ እራሳችን ጥሩ እና ቀና አመለካከት እንዲኖረን መጣር፡፡
- ሕክምና የጀመርን ከሆነ የሐኪም ትዕዛዝን መአግባቡ መከተል፡፡
